+ ገድለ አባ በግዑ + ሰምታችሁ በረከትን አግኙ
HTML-код
- Опубликовано: 9 фев 2025
- የቅዱሳን ታሪክ / Yekidusan Tarik የፌስቡክ ገፅ
- / %e1%8b%a8%e1%89%85%e1%...
+++አባ በግዑ+++
አባ በግዑ፡- አባ በግዑ በመጀመሪያ ሽፍታ የነበረ ሲሆን በመንገድ ላይ ንብረት የያዘን ሰው ማንንም የማያሳልፍ ቀማኛ ሰው ነበር፡፡ ከኃይለኛነቱ የተነሳ ሕዝቡም ሁሉ ይፈራው ነበር፡፡ በእጁ ሰይፍና ጦር ይዞ ሊዘርፍ ወደ ወደደው ሀገር ይገባል፡፡ እየዘረፈ በሚያገኘው ገንዘብም ራሱን በተለያዩ ምግቦችና መጠጦች ያስደስት ነበር፡፡ ባማሩ ልብሶችም ይዋብ ነበር፡፡ ገንዘቡ የተወሰደበት ሰውም እርሱ እንደወሰደበት ባወቀ ጊዜ ዳግመኛ መጥቶ የተረፈውን ቀምቶ እንዳይወስድበት ምንም አይከሰውም ነበር፡፡ በጉልምስናው ኃይለኛና ብርቱ ስለነበር ወደ እርሱ ማንም አይቀርብ ነበር፡፡
በእንደዚህ ያለ የውንብድና ሥጋ ብዙ ዓመታት ከኖረ በኋላ አባ በግዑ በስም ክርስቲያን ነበረና ከዕለታት በአንደኛው ቀን መንፈስ አነሳስቶት ወደ ቤተ ክርስቲያን ሄደ፡፡ ካህኑም ባየው ጊዜ ከመንገድ ገለል አደረገውና ‹‹የሕይወት ዘመንህን ሁሉ በከንቱ አሳለፍክ ዛሬ ስማ ልንገርህ፣ በዘመንህ ፍጻሜ እግዚአብሔር ይጎበኝሃል፣ በመንፈስ ቅዱስም ያድርብሃል፣ ፍጹም መነኩሴ ትሆናለህ፣ በብዙ መከራና ተጋድሎ ትኖራለህ በዚያም የነፍስህ መዳኛ ይሆናል፣ እግዚአብሔርንም ደስ ታሰኘዋለህ›› አለው፡፡ ከዚህም የበዛውን ብዙ ነገር ነገረው፡፡
ከዚህም በኋላ ወደ ቤተ ክርስቲያን ገብቶ ቁርባን ተቀበለ፡፡ ወደቤቱም ከተመለሰ በኋላ ካህኑ የነገሩትን እያሰበ ‹‹እስከመቼ በስንፍናዬ እኖራለሁ? እስከመቼስ የነፍሴን መዳኛ ሳላስብ እኖራለሁ? …›› እያለ አሰበ፡፡ ከዚህም በኋላ ከዘመዶቹ ተለይቶ ከሀገሩ ወጥቶ ሄደና ወደ ባሕር ዳርቻ ደርሶ የቅዱስ እስጢፋኖስን ቤተ ክርስቲያን እጅ ነሣ፡፡ ከመነኮሳትም ማኅበር ገብቶ እነርሱን ማገልገል ጀመረ፡፡ አባ በግዑ በእግዚአብሔር ጥሪ ወደ ልቡ ተመልሶ ከመነነ በኋላ ግን እስከሞተበት ዕለት ድረስ የላመ እህል ሳይቀምስ ኖረ፡፡ ምግቡን የዛፍ ፍሬና ሜዳ ላይ የሚበቅል ቅጠል አደረገ፡፡ ዓቢይ ጾም ሲመጣም ከሰኞ እስከ ቀዳሚት ሰንበት ምንም ሳይቀምስ የሚጾም ሆነ፡፡ ውኃንም ሳይጠጣ ኖረ፣ ማንም ሰው ሳያውቅብ ለ5 ወር ምንም ውኃ ሳይጠጣ ተቀመጠ፡፡
ከ5 ወር በኋላም የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል ወደ አባ በግዑ መጣና ‹‹የእግዚአብሔር ሰው ሰላም ለአንተ ይሁን! በምን ትታወካለህ? ምንስ ያሳዝንሃል? ››አለው፡፡ አባ በግዑም ‹‹ጌታዬ ከውኃ ጥም የተነሣ በጣም ስለተጨነቅሁ ነው›› አለው፡፡ መልአኩም ነጥቆ ወደ ገነት ወሰደውና ከገነት ቅጠል አንሥቶ አቀመሰው፡፡ ወዲያም የአባ በግዑ ሰውነት ታደሰች፡፡ ከዚህም በኋላ ‹‹ውኃ ሳልጠጣ ተጋድሎዬን እፈጽም ይሆን!›› የሚለው የኅሊና መታወክ ከእርሱ ጠፋለት፡፡
ከዕለታትም በአንደኛው ቀን አባ በግዑ ለሚወደው ለአንድ ወዳጁ ለማንም እንዳይናገር በእግዚአብሔር ስም ካስማለው በኋላ ለ5 ወር ምንም ውኃ እንዳልጠጣ ምሥጢሩን ነገረው፡፡ ያ ወዳጁም ይህን ሲሰማ ደንግጦ አለቀሰ፡፡ አባ በግዑም አብሮት አለቀሰ፡፡ ወዳጁም ‹‹እስከዛሬ ከውኃ የተከለከለ በማን ዘንድ ሰማህ? አሁንም ቅዱሳን መነኮሳትና አበ ምኔቱ አያምኑህም፡፡ ይህን ምሥጢር ዛሬ ብሸሽግ በመጨረሻ ይገለጣል፡፡ ሕዝቡ፣ ነገሥታቱና መኳንንቱም ይህን ነገር ይሰማሉ ነገር ግን አያምኑም፡፡ አሁንም የምነግርህን ስማኝና ትኅርምቱን ትተህ ውኃ ጠጣ›› አለው፡፡ የእግዚአብሔር ሰው አባ በግዑም ‹‹የነገርከኝ ሁሉ እውነት ነው ሐሰት የለውም ነገር ግን እኔ ከዚህ በኋላ እስክሞት ድረስ ዳግመኛ ውኃ እንዳልጠጣ ስለ እግዚአብሔር ትቻለሁ፡፡ ሰዎች ባያምኑ እኔ ምን ገዶኝ፣ ነገር ግን በዚህ ገድል እግዚአብሔር ረዳት ይሆነኝ ዘንድ ጸልይልኝ›› አለው፡፡
ከዚህም በኋላ የእግዚአብሔር ሰው አባ በግዑ ብረት አመጣና ሰንሰለቶችን ይሠራለት ዘንድ ለአንጥረኛ ሰጥቶ አሠራ፡፡ ያንን ወዳጁን ጠራውና እጆቹንና እግሮቹን በብረት ችንካር እንዲያስረው አዘዘው፡፡ ‹‹አበ ምኔቱን ጥራልኝ›› አለውና ጠራለት፡፡ አባ በግዑም አበ ምኔቱ አቡነ ኢየሱስ ሞዐ ሲመጣ በፊቱ ሰገደለትና ‹‹አባቴ ሆይ! የእግዚአብሔርን ትእዛዝ እፈጽም ዘንደ በላዬ ላይ ጸልይልኝ›› አለው፡፡ ‹‹ከዛሬ ጀምሮ ከበዓቴ አልወጣም፣ ሰውም ወደኔ አይገባም›› አለው፡፡ አቡነ ኢየሱስ ሞዐም በላዩ ከጸለየለት በኋላ ‹‹ለእኔም ጸልይልኝ›› አለው፡፡ አባ በግዑም በቅዱስ ሚካኤል በዓል ቀን በአባ ኢየሱስ ሞዐ እጅ ቁርባንን ከተቀበለ በኋላ እጆቹንና እግሮቹን በብረት ችንካር ታስሮ ብቻውን ዘግቶ በጽኑ የተጋድሎ ሕይወት ኖረ፡፡ በዓቱንም ዙሪያውን መውጫ መግቢያ እንዳይኖረው መረገው፡፡ ለምግብ የሚሆነውን የዛፍ ፍሬና የሜዳ ቅጠል ማስገቢያ የሚሆን ትንሽ ቀዳዳን አበጃና ያ ወዳጁ ያስገባለታል፡፡ አባ በግዑም ያንን በሦስት ቀን አንድ ጊዜ ብቻ ይመገባል፡፡
የእግዚአብሔር ሰው አባ በግዑ በእንዲህ ዓይነት ጽኑ በሆነ የተጋድሎ ሕይወት ሲኖር ሰውነቱ ላይ ከቆዳውና ከአጥንቱ በቀር የሚታይ ነገር እስኪጠፋ ድረስ ታላቅ ተጋድሎን ተጋደለ፡፡ ውኃንም እስከ ሰባት ዓመት ድረስ አልጠጣም፡፡ መቆምም አይችልም ነበርና መነኮሳቶቹ ለቁርባን በቃሬዛ አድርገው ወደ ቤተ ክርስቲያን ይወስዱት ነበር፡፡ የእግዚአብሔር ሰው አባ በግዑ በእንደዚህ ዓይነቱ ለመስማት በሚከብድ እጅ የበዛ ጽኑ ተጋድሎ ካደረገ ከብዙ ድካም በኋላ በዚህች ዕለት ታህሳስ 27 ቀን ዐረፈ፡፡ ጌታችንም ተገልጦ ታላቅ ቃልኪዳን ሰጠው፡፡ የአባ በግዑ ረድኤት በረከቱ ይደርብን በጸሎቱ ይማረን፡፡
ወዳጆች ሆይ! ይህንን ማን ያምናል!? ለሰው ምንም ውኃ ሳይጠጣ ሰባት ዓመት መኖር ይቻለዋልን!? ‹‹በብዙ ሲጋደሉ እንደኖሩ የቅዱሳንን ገድላቸውን ሰምተናል፡፡ ነቢይ ዕዝራ የዱር ዛፍ ፍሬ እየተመገበ ውኃም እየጠጣ በምድረ በዳ እየጾመ ኖረ፡፡ ነቢይ ኢሳይያስም የሜዳ ጎመን እየቆረጠ ከእርሱም እየተመገበ ውኃም እየጠጣ በተራራ እየጾመ ኖረ፡፡ እግዚአብሔር ስሙን ‹የበረሃ ኮከብ› ብሎ የጠራው የመነኰሳት በኩር የሆነ አባ እንጦንስና አባ መቃርስም በደረቅ ኅብስትና በውኃ ብቻ ሲጋደሉ ኖሩ፡፡ እኚህ ምድራዊያን ሲሆኑ ሰማያውያን ሆኑ፡፡ ነቢይ ኤልያስም በኅብስትና በውኃ ብቻ በምድረ በዳ ሲጋደል ኖረ፡፡ ይህ የእግዚአብሔር ሰው አባ በግዑ ግን ሰባት ዓመት ሙሉ ውኃ ሳይቀምስ ኖረ፡፡ ከመነነ በኋላ እስከሞተበት ዕለት ድረስ እህል የሚባል አልቀመሰም፡፡ እርሱ ግን ራሱን በእግዚአብሔር ፊት ዝቅ ያደርግና በትህትናም ሆኖ ስለ ኃጢአቱ ሁልጊዜ ያለቅስ ነበር፡፡
ይህም የእግዚአብሔር ሰው አባ በግዑ ይህን ሁሉ የተጋደለ በራሱ ኃይል አይደለም፤ በእግዚአብሔር ኃይል ነው እንጂ፡፡ አንተም ወንድሜ ሆይ ራስህን ዕወቅ፡፡ ምንም ተጋድሎን ብታደርግ ጾምኩ፣ ተራብኩ፣ ስለ እግዚአብሔርም ብዬ ራሴን አደከምኩ፣ እግዚአብሔርንም ስላገለገልኩ በሥራዬም እድናለሁ አትበል፡፡ መጨረሻህን አታውቅም፡፡ አንተ ግን ስለ እግዚአብሔር ብለህ ራስህን ኃጥእ አድርግ ያን ጊዜ እግዚአብሔር ያጸድቅሃልና፡፡ ወዳጄ ሆይ በእግዚአብሔር ዘንድ እንድትመሰገን ራስህን አታመስግን፤ ሌሎችም ያመሰግኑህ ዘንድ አትውደድ፡፡ ክብር ታገኝ ዘንድ ትሕትናን ገንዘብ አድርግ፡፡›› (ገድለ አባ በግዑ)